|
አልሸባብ 10 ወታደሮች ገደልኩ ብሏል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥር 21 ቀን 2004 ዓ.ም. January 25, 2012)፦ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ሰፈር ላይ የአልሸባብ አጥፍቶ ጠፊ በሚኒባስ ሙሉ የታጨቁ ቦምቦች ማፈንዳቱ ተዘገበ። በጥቃቱ 10 የኢትዮጵያ ወታደሮች መግደሉን አልሸባብ ገለጸ።
“ፍንዳታው መላ ከተማዋን ያንቀጠቀጠ ነበር። አጥፍቶ ጠፊው ወደ ጦር ሰፈሩ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በጠባቂዎች ቢተኮስበትም በሩ ላይ ግን ሊያፈነዳው ችሏል።” ሲሉ የአካባቢው የደህንነት ሹም የሆኑት መሀመድ ኦስማን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና አውታር መስክረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በአልሸባብ መሆኑንም ማንነታቸውን ያልገለጹ የቡድኑ ቃል አቀባይ አንዱለስ በተባለው ሬድዮ አማካኝነት ይፋ አድርገዋል።
በፍንዳታው 10 የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸውን አልሸባብ የገለጸ ቢሆንም የአካባቢው የደህንነት ባለስልጣን ግን ገና ምርመራ በማድረግ ላይ ነን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ጦር እየተገለገለበት የነበረው የመንግስት ህንጻ በጥቃቱ በአብዛኛው መደርመሱን የአይን ምስክሮች ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ዳግም ወደ ሱማሊያ የገባው በቅርቡ ሲሆን ይህ ጥቃት የተፈጸመባትንና ከኢትዮጵያ ድንበር ወደ ሞቃዲሾ በሚወስደው ዋናው መንገድ ላይ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በለደወይን የተባለችውን ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ምቹ (ስትራቴጅካዊ) የተባለችውን ከተማ የተቆጣጠረውም ባለፈው ሳምንት ነበር። መንግስት የኢትዮጵያ ጦር የተቆጣጠራቸውን ስፍራዎች ለአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አስረክቦ እንደሚወጣ ቢገልጽም ይህ መቼ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ግን የተገለጸ ነገር የለም።
|