|
4 ሰዎች ታግተዋል፣ ሁለት ቆስለዋል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም. January 18, 2011)፦ ትላንት ማክሰኞ ከጠዋቱ 5 ሰዓት ላይ በአፋር ክልል ያልታወቁ ታጣቂዎች በወሰዱት ርምጃ የተገደሉት አምስት ጎብኝዎች ዜግነት መረጋገጡ እና አራት ሰዎች መታገታቸው ታወቀ።
ቀደም ሲል ጥቃቱ የደረሰው 8 ሆነው በሚጓዙ የቱሪስቶች ቡድን ላይ ነው ሲል የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መዘገቡ ቢታወቅም የኮሚኒኬሽን ሚኒስተር የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን ግን የጎብኝዎቹ ቁጥር ከዚያ በላይ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
ድርጊቱ የተፈጸመው 27 የጎብኝዎች ቡድን ላይ መሆኑን የዜና አውታሮች የጠቀሱ ሲሆን ጥቃት ከተፈጸመባቸው ጎብኝዎች መሀል የኦስትሪያ፣ የቤልጂዬም፣ የጀርመን፣ የሀንጋሪና የኢጣሊያ ዜግነት ያላቸው እንደሚገኙበት ከመገለጹም በላይ ሟቾቹ ሁለት ጀርመናዊያን፣ ሁለቱ ደግሞ ሀንጋሪያዊያን እና አንድ ኦስትሪያን መሆናቸው ታውቋል።
ታግተው ከተወሰዱት አራት ሰዎች መሀል ሁለቱ የውጭ ሀገር ዜጎች ጀርመናዊያን ሲሆኑ ሲሆኑ ሹፌሩንና አንድ ፖሊስን ጨምሮ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውም ተገልጿል። ቁስለኞቹም አንድ የሀንጋሪ ተወላጅና አንድ ኢጣሊያዊ መሆናቸው ታውቋል።
አቶ በረከት ስምኦን ጥቃቱ የተፈጸመው ከኤርትራ ድንበር በ20 እና በ25 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ነው ያሉ ሲሆን ታጣቂዎቹ ኤርትራ ሰልጥነው የመጡ ናቸው በሚልም የኤርትራን መንክስት ወንጅለዋል።
በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ግርማ አስመሮም ግን ክሱ “የለየለት ውሸት ነው። ጥቃቱም የኢትዮጵያ የውስጥ ችግር እንጂ እኛን የሚመለከት አይደለም።” ሲሉ አስተባብለዋል።
|