|
አስገድዶ መድፈርና ከፍተኛ የመብት ረገጣ ተፈጽሞባቸዋል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም. January 18, 2011)፦ በኢትዮጵያ ለም የሆኑ የእርሻ መሬቶችን ለኢንቨስትመንት ለመስጠት መንግስት በያዘው ፕሮግራም ሳቢያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች በግዳጅ እየተነሱ ለኑሮ ተስማሚ ወዳልሆኑ ቦታዎች መወሰዳቸውን ሂዩማን ራይትስ ወች አጋልጧል።
ባለፈው አመት በጋምቤላ ክልል ብቻ 70ሺህ ኢትዩጵያዊያን ያላንዳች ምክክርና ካሳ ከመሬታቸው ላይ እየተነሱ በግዳጅ ወደተለያዩ የሰፈራ መንደሮች እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን በሂደቱም ማስፈራራትና እንግልት እየተፈጸመባቸው እንደሆኑና በእምቢተኝነታቸው የጸኑ ነዋሪዎችም እንደታሰሩ ተገልጿል።
ይህንኑ በተመለከተ በ5 የተለያዩ የጋምቤላ ወረዳዎች ነዋሪ የነበሩ ከ100 በላይ ሰዎችናና በስደት ወደ ኬንያ የተሻገሩ የአካባቢው ነዋሪዎችን አነጋግሮ ሪፖርቱን ያጠናቀረው ተቀማጭነቱ በኒው ዮርክ የሆነው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እርምጃው መንግስት እንደሚለው ለነዋሪዎቹ ምቾት ሳይሆን መሬታቸውን ለመቸብቸብ በመፈለግ የተወሰደ እርምጃ ስለመሆኑ ያለውን እምነት ይፋ አድርጓል።
በ2007 ዓ.ም የተደረገው የህዝብ ቆጠራ የጋምቤላ ነዋሪዎች ብዛት 307 ሺህ መሆናቸውን መግለጹ ሲታወስ አሁን እየተወሰደ ያለው ርምጃ ከአጠቃላዩ የክልሉ መሬት 42 በመቶ የሚሆነውን ለኢንቨስተሮች አሳልፎ በሊዝ ለመስጠት በመንግስት የተያዘው ፕሮግራም አካል መሆኑ ታምኖበታል።
የሂዩማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት ተመርኩዘው የተለያዩ አለም አቀፍ የዜና ምንጮች ሰፋፊ ዘገባዎችን ያቀረቡ ሲሆን መንግስት ነዋሪዎቹን ከመሬታቸው ለማንሳት አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ከብቶቻቸውን በመግደልና መኖሪያ ቤታቸውን በማቃጠል ከባባድ የመብት ረገጣዎች መፈጸሙን ዋሽንግተን ፖስት ይፋ አድርጓል።
ሮይተርና ብሉምበርግ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ለ24 የተለያዩ ኢንቨስተሮች በድምሩ 3.6 ሚሊየን ለም መሬት በሊዝ መስጠቷን አጣቅሰው ይኸውም ከቤልጂዬም የቆዳ ስፋት ጋር የሚመጣጠን ነው ብለዋል። መንግስት ተጨማሪ 2.1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለኢንቨስተሮች በሊዝ ለማቅረብ እቅድ ያለው ሲሆን የጋምቤላ ነዋሪ የሆኑት የኑዌርና አኝዋክ ጎሳዎችን በዚህ ጦስ እየታመሱ ይገኛሉ።
እየተገደዱ የተዛወሩባቸው መንደሮች በቂ የህክምና፣ የትምህርትም ሆነ መሰል ወሳኝ ተቋማት ያልተሟሉባቸው ሲሆን ከፍተኛ የምግብ እጥረት በመኖሩም በረሀብ አለንጋ እየተገረፉ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።
የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ሽፈራው ተ/ማሪያም ግን እስካሁን ከጋምቤላ 20ሺህ ቤተሰቦች ወይንም 100ሺህ ሰዎች ወደ ሰፈራ መንደሮች መዛወራቸውንና በመጭዎቹ ሁለት አመታት ሌሎች 25ሺህ ቤተሰቦች እንደሚዛወሩ ቢያምኑም ዝውውሩ በውዴታ እንጂ በግዳጅ አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እውቁ የሰበአዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ወች ያወጣውን ሪፖርት የፖለቲካ አላማ ያለውና የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር ታቅዶ የቀረበ የውሸት ሪፖርት ነው ሲል ሊያጣጥለው የሞከረ ቢሆንም የተለያዩ የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የወዳጅ መንግስታት ተወካዮችም ጭምር ከመንግስት ርምጃ ተቃርነው ቆመዋል።
በእንግሊዝ የዓለማቀፍ ዲቨሎፕመንት ሚኒስትር የሆኑት አንድሪው ሚቸል “በኢትዮጵያ የብሪቲሽ መንግስት የልማት ርዳታ ይህን የሰፈራ መንደር ፕሮግራም አይደግፍም። አያበረታታም።” ያሉ ሲሆን ለማህበረሰቡ የተገቡለት ቃሎች አልተከበሩም የሚለውን የሂዩማን ራይትስ ዎችን ክስም እንደሚጋሩት ገልጸዋል።
መንግስት ለም መሬቶችን በሊዝ ለመቸብቸብ በያዘው ፕሮግራም በድምሩ 1.5 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩበት መሬት እየተፈናቀሉ ወደተለያዩ የሰፈራ መንደሮ ሊዛወሩ እንደሚችሉ የሰበአዊ መብት ተሟጋቹ በሪፖርቱ ጠቁሟል።
|