Home ዜና Latest በቤጂንግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳተፉባቸው ሦስት ውድድሮች ማጣሪያውን አለፉ
 
በቤጂንግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳተፉባቸው ሦስት ውድድሮች ማጣሪያውን አለፉ Print E-mail
Saturday, 16 August 2008 20:19

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ነኀሴ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. August 16, 2008)፦ በቤጂንጉ ኦሎምፒክ በትናንትናው እና በዛሬው ዕለት በተደረጉት በወንዶች የ1,500 ሜትር መሰናልክ እና የ3,000 ሜትር መሰናክል እንዲሁም በሴቶች የ3,000 ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያ ማጣሪያውን አለፈች።

 

የወንዶች 1500 ሜትር መሰናክል

 

ትናንት ዓርብ ነኀሴ 9 ቀን 2000 ዓ.ም. በአራት ምድብ በተደረጉት የወንዶች 1,500 ሜትር መሰናክል የማጣሪያ ውድድሮች ላይ ሦስት ኢትዮጵያውያን ተሳትፈው፤ ሁለቱ ማጣሪያውን አልፈዋል።

 

ከምድብ አንድ አትሌት ደረሰ መኮንን በ3:36.22 ደቂቃ ውድድሩን በ5ኛ ደረጃነት አጠናቅቆ ከምድቡ ካለፉት 5 አትሌቶች ውስጥ አንዱ ሆኗል።

 

በምድብ ሦስት የተካፈለው አትሌት ደማ ዳባ ደግሞ ውድድሩን በ3፡37.78 ደቂቃ በመጨረስ 8ኛ የወጣ ሲሆን፣ ማጣሪያውን ሳያልፍ ቀርቷል።

 

በምድብ አራት የተወዳደረው አትሌት ሙሉጌታ ወንድሙ በ3፡36.67 ደቂቃ ውድድሩን ጨርሶ 7ኛ የወጣ ሲሆን፣ የተሻለ ሰዓት በማስመዝገቡ የማጣሪያ ውድድሩን አልፏል።

 

የወንዶች 1,500 ሜትር መሰናክል የፍፃሜ ውድድር የፊታችን ማክሰኞ ነኀሴ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 19, 2008) በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 11፡50 ሰዓት (5:50 PM / 17:50) ላይ ይካሄዳል።

 

በዚህ ርቀት የዓለም ክብረወሰን ያለው በሞሮኳዊው ሒካም ኤል ጉሮዥ ሲሆን፣ ጁላይ 14 ቀን 1993 እ.ኤ.አ. ሮም - ጣሊያን ላይ ርቀቱን በ3፡26.00 ደቂቃ ጨርሶታል። የኦሎምፒክ ክብረወሰን ደግሞ 3፡32.07 ደቂቃ ሲሆን፣ ኬኒያዊው ኖሕ ነጅኒ፣ ሲድኒ - አውስትራሊያ ላይ ሴፕቴምበር 29 ቀን 2000 እ.ኤ.አ ያስመዘገበው ነው።

 

የሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል

 

የሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል የተካሄደው ትናንት ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ወክለው የተሰለፉት አትሌቶች ዘምዘም አሕመድ፣ መቅደስ በቀለ እና ሶፊያ አሰፋ ነበሩ። በምድብ ሦስት የተካፈለችው አትሌት ዘምዘም አሕመድ ውድድሩን በ9፡25.63 ደቂቃ በመጨረስ 4ኛ በመውጣት ማጣሪያውን አልፋለች።

 

በምድብ አንድ የተካፈለችው መቅደስ በቀለ በ9፡41.43 ደቂቃ በመግባት 9ኛ ስትወጣ፣ በምድብ ሁለት ደግሞ ሶፊያ አሰፋ በ9፡47.02 ደቂቃ 8ኛ የወጣች ሲሆን፣ ሁለቱም አትሌቶች የማጣሪያ ውድድሩን አላለፉም።

 

ነገ እሁድ ነኀሴ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 17, 2008) የሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል የፍፃሜ ውድድር በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 10፡30 ሰዓት (4:30 PM / 16:30) ላይ ይካሄዳል።

 

የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን 9፡01.59 ደቂቃ ሲሆን፣ ራሻዊቷ ጉልናራ ጉልኪና-ሳሚቶቫ ጁላይ 4 ቀን 2004 እ.ኤ.አ. ሔራክሊዮን ግሪክ ላይ ያስመዘገበችው ነው።

 

የወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል

 

የወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል በሦስት ምድብ የተካሄደው ዛሬ ጠዋት ሲሆን፣ ከሦስቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውስጥ በምድብ ሁለት የተሳተፈው አትሌት ያዕቆብ ጃርሶ ውድድሩን በ8፡16.88 ደቂቃ በመጨረስ በአንደኝነት ያጠናቅቆ ማጣሪያውን አልፏል።

 

በምድብ አንድ አትሌት ናሆም መስፍን በ8፡23.82 ደቂቃ ውድድሩን ጨርሶ 5ኛ ሲወጣ፣ በምድብ ሦስት ደግሞ አትሌት ሮባ ጋሪ በ8፡28.27 ደቂቃ 8ኛ ወጥቷል። አትሌት ናሆምና አትሌት ሮባ ለፍፃሜው ሳያልፉ ቀርተዋል።

 

በዚሁ ርቀት የፍፃሜው ውድድር የሚካሄደው ሰኞ ነኀሴ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 18, 2008) በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 10፡10 ሰዓት (4:10 PM / 16:10) ላይ ነው።

 

የወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረወሰን 7፡53.63 ደቂቃ ሲሆን፣ ሴፕቴምበር 3 ቀን 2004 እ.ኤ.አ. ብራስልስ - ቤልጅየም ላይ ኳታራዊው ሳይፍ ሰዒድ ሻኸን ያስመዘገበው ነው። የኦሎምፒኩ ክብረወሰን ደግሞ 8፡05.51 ደቂቃ ሴኦል - ኮሪያ ላይ ሴፕቴምበር 30 ቀን 1988 እ.ኤ.አ. በኬንያዊው ጁልየስ ካሪኡኪ የተመዘገበው ነው። (ቀሪዎቹን ውድድሮች ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድና ቀሪዎቹን የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድር ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድ ያዘጋጀነውን የውድድሩን የጊዜ ሠሌዳ እዚህ በመጫን ያገኙታል!)

 

 

 

አዲስ ዜናዎችና ጽሑፎች