Home ዜና ፎርቹን ጋዜጣ በፕሬስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 20 ሚሊዮን ብር ካሣ እንዲከፍል ክስ ቀርቦበታል
ፎርቹን ጋዜጣ በፕሬስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 20 ሚሊዮን ብር ካሣ እንዲከፍል ክስ ቀርቦበታል PDF Print E-mail
Friday, 18 July 2008 12:52

ፎርቹን ጋዜጣ ከአንበሳ አውቶቡስ ክስ በነፃ ተሰናበተ

የአያት እና የሣባ ኢንጂነሪንግ ክስ ይቀረዋል

Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. July 18, 2008)፦ በግል ፕሬስ ታሪክ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ20 ሚሊዮን ብር የካሣ ጥያቄ ክስ የተመሰረተበት ”ፎርቹን” የተባለው ሀገር ውስጥ የሚታተመው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በስም ማጥፋት ከቀረቡበት ሦስት ክሶች የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ ክስን ሲረታ፤ የአያት ሪል ስቴት ክርክር እንዲቀጥል ትዕዛዝ የተሰጠበት ሲሆን፣ ለሣባ ኢንጂነሪንግ ክስ ደግሞ መልስ አቅርቧል።

 

የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ሚያዝያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. ባቀረበው የክስ አቤቱታ ፎርቹን ”Fortune” የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በቅፅ 8 ቁጥር 398 ታህሣሥ 6 ቀን 2000 ዓ.ም. ባወጣው ዕትሙ ላይ ”Anbessa city buses Loses third manager in six month”፣ ”አንበሳ የከተማ አውቶቡስ በስድስት ወራት ውስጥ ሦስት ሥራ አስኪያጆችን አጣ” በሚል ርዕስ ስር ሐሰተኛ ዜና በማውጣት የድርጅቱን መልካም ስም አጉድፏል በሚል የ120 ሺህ ብር የካሣ ክፍያ እንዲከፈለው በማመልከት ክስ መስርቶ ነበር።

 

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሳሽና ተከሳሽን በፍሬ ነገር ካከራከረ በኋላ፣ ሰኔ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. በሰጣቸው የፍርድ ውሳኔ፤ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ጋዜጣው ያወጣው ዘገባ ሐሰተኛ ነው የሚልበትን ምክንያት ከመዘርዘርና እውነተኛው ነገር ምን እንደሆነ ለማሳየት ያስችላሉ ያላቸውን ማስረጃዎች ከማቅረቡ በቀር፣ ጋዜጣው ዘገባውን በማውጣቱ የተነሳ፤ ድርጅቱ የተጠላ፣ የተዋረደ ወይም የተሳቀበትና በእርሱ ላይ የነበረ እምነትና መልካም ዝና ወይም የወደፊት ዕድል የተበላሸ ስለመሆኑ ያቀረበው አንድም ማስረጃ ባለመኖሩ ክሱ ውድቅ ሆኖ ጋዜጣው በስም ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ ነው ሳይባል በነፃ ተሰናብቷል። በኅትመቱ ላይም ማስተባበያ ለማወጣትም ሆነ ካሣ ለመክፈል አይገደድም ብሏል።

 

በሌላ በኩል በግሉ ፕሬስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የ20 ሚሊዮን ብር ካሣ እንዲከፍል የሚጠይቅ ክስ የቀረበበት ፎርቹን ጋዜጣ ፍርድ ቤቱ ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ክርክሩ ይቀጥል ብሏል።

 

ፍርድ ቤቱ በዚሁ ዕለት በሰጠው ብይን ጋዜጣው ያቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ክርክሩ ይቀጥል ሲል ወስኗል።

 

በሚቀጥለው ቀጠሮም አያት ሪል ስቴት ስሜ ጠፍቷል በማለት ክስ የመሰረተበት ጋዜጣ “ምን ያህሉ ግለ ሃሳብ ናቸው”፣ “ምን ያህሉ ደግሞ ፍሬ ነገር ላይ የተመለከቱ ናቸው”፣ “ፍሬ ነገሩ ላይ ያተኮሩ ናቸው” ከተባለ ደግሞ፣ “ፍሬ ነገሮቹ እውነት አላቸው የላቸውም”፣ “እውነትነት የሌላቸው ከሆኑ ደግሞ ሆን ተብለው የተደረጉ ናቸው አይደሉም”፣ “ክሱ የፕሬሱን ድርጅት ብቻ ነው ወይስ ሁሉንም ተከሳሾች ይመለከታቸዋል? ከተመለከታቸውስ በምን ያህል ድርሻ ነው” በሚለው ጭብጥ ላይ ክርክር ለማድረግ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

 

በተያያዘም ሳባ አንጅነሪንግ ፒ.ኤል.ሲ. የተባለው ኩባንያ በጋዜጣው ላይ ለመሰረተው ክስ ፎርቹን መልስ ሰጥቶ ለቀጣዩ ችሎት ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

 

 
 

በጽሑፍ መሳተፍ ለምትፈልጉ በሙሉ!

በማናቸውም ጉዳይ ላይ ያለዎትን ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ትችት፣ ግጥም፣ ልብወለድ፣ … በማይክሮሶፍት ወርድ ፕሮግራም በዩኒኮድ ፎንት ጽፈው ከራስዎ ኢ-ሜይል ሳጥን ጽሑፎትን አያይዘው በኢ-ሜይል አድራሻችን ethiopiazare@gmail.com ቢልኩልን ለሥራችን ቅልጥፍና ይረዱናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ