Home ዜና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የላዕላይ ም/ቤት ነገ ይሰበሰባል
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የላዕላይ ም/ቤት ነገ ይሰበሰባል PDF Print E-mail
Saturday, 17 May 2008 08:57

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2000 ዓ.ም. May 17, 2008)፦ በወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው የቀድሞው የቅንጅት ፓርቲ፣ የአሁኑ የ”አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ” በነገው ዕለት የላዕላይ ም/ቤቱ ተሰብስቦ ፓርቲው ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት ያስችለው ዘንድ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎች ላይ እንደሚደርስ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ላዕላይ ምክር ቤቱ በነገው ዕለት በሚያደርገው ስብሰባ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ መቼ እንደሚጠራ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህም ሌላ ጠቅላላ ጉባዔው የት እንደሚደረግ፣ በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ፣ … እንደሚወስን እነኝሁ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አስረድተዋል።

 

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ዛሬ እንደዘገብነው ከሆነ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ የተሰኘው ፓርቲ እስካሁን ድረስ ሕጋዊ እውቅና ከምርጫ ቦርድ አለማግኘቱ ይታወቃል። ከዚህም ሌላ ፓርቲው ሕጋዊ ፈቃድ እና እውቅና እንዲሰጣቸው ለምርጫ ቦርድ ማመልከቻ እንዳላስገቡ ይታወቃል።

 

በነገው ዕለት የሚሰበሰበው የላዕላይ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔው የሚደረግበትን ቀን ወስኖ ሲያበቃና ጠቅላላ ጉባዔው ሲካሄድ ፓርቲው ሊቀመንበሩን፣ ምክትል ሊቀመንበሩን፣ ዋና ፀሐፊውን፣ የሕዝብ ግንኙነቱን፣ … በአጠቃላይ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራር አባላት እና አካላት እንደሚመርጥ ይጠበቃል።

 

አንድነት ለዴሞክራሰና ለፍትህ የፓርቲውን አመራሮች መርጦ ሲያበቃና ምርጫ ቦርድ የሚጠይቃቸውን ፎርማሊቲዎች አሟልቶ ሲያጠናቅቅ የፓርቲውን ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት ለምርጫ ቦርድ ማመልከቻ እንደሚያስገባ ለማወቅ ችለናል።

 

ተያያዥ

 

በጽሑፍ መሳተፍ ለምትፈልጉ በሙሉ!

በማናቸውም ጉዳይ ላይ ያለዎትን ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ትችት፣ ግጥም፣ ልብወለድ፣ … በማይክሮሶፍት ወርድ ፕሮግራም በዩኒኮድ ፎንት ጽፈው ከራስዎ ኢ-ሜይል ሳጥን ጽሑፎትን አያይዘው በኢ-ሜይል አድራሻችን ethiopiazare@gmail.com ቢልኩልን ለሥራችን ቅልጥፍና ይረዱናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ