Home ዜና ፕሮፌሰር መስፍን በነፃ ተሰናበቱ
ፕሮፌሰር መስፍን በነፃ ተሰናበቱ PDF Print E-mail
Tuesday, 06 May 2008 10:25

Prof. Mesfin W/MariamEthiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2000 ዓ.ም. May 6, 2008)፦ በ1993 ዓ.ም. ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሕገ-ወጥ ቅስቀሳ በማድረግ ረብሻ አነሳስተዋል በሚል ቀርቦባቸው ከነበረው ክስ በነፃ መሰናበታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ዘገበ።

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በ1993 ዓ.ም. ህወሓት የተሰነጠቀ ሰሞን ሁለት ክሶችን በጋራ መከሰሳቸው አይዘነጋም። አንደኛው ክስ ‘በሕገ-ወጥ መንገድ ፓርቲ አቋቁማችኋል’ የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ‘ህዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳሳ በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለአመጽና ለረብሻ የሚያነሳሳ ንግግር አድርጋችኋል” የሚሉ ነበሩ።

 

በወቅቱ ሁለቱም ታስረው በዋስ ከተለቀቁ በኋላ በውጭ ሆነው ሲከራከሩ የቆዩ ሲሆን፣ ከቅንጅት አመራሮች ጋር በእስር በነበሩበት ጊዜም ፍርድ ቤት እየቀረቡ ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ነበር።

 

በወቅቱ በእስር ላይ እያሉም የካቲት 27 ቀን 1999 ዓ.ም. በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ችሎት ቀርበው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን በሁለቱም ክስ ፍርድ ቤቱ በነፃ አሰናብቷቸዋል። ፕሮፌሰር መስፍንን ደግሞ ‘በሕገ-ወጥ መንገድ ፓርቲ አቋቁማችኋል’ ከሚለው ክስ በነፃ አሰናብቷቸው በሁለተኛው ክስ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል።

 

ፕሮፌሰር መስፍን እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶባቸው በነበረው ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሕገ-ወጥ ቅስቀሳ በማድረግ ረብሻ አስነስተዋል በሚለው ክስ ሲከራከሩና ሲከላከሉ ቆይተዋል። በዛሬው ዕለት (ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2000 ዓ.ም.) በተሰጠው የፍርድ ውሳኔ፤ ፕሮፌሰር መስፍን ክሱን በሚገባ ስላስተባበሉ በነፃ ተሰናብተዋል።

 
 

በጽሑፍ መሳተፍ ለምትፈልጉ በሙሉ!

በማናቸውም ጉዳይ ላይ ያለዎትን ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ትችት፣ ግጥም፣ ልብወለድ፣ … በማይክሮሶፍት ወርድ ፕሮግራም በዩኒኮድ ፎንት ጽፈው ከራስዎ ኢ-ሜይል ሳጥን ጽሑፎትን አያይዘው በኢ-ሜይል አድራሻችን ethiopiazare@gmail.com ቢልኩልን ለሥራችን ቅልጥፍና ይረዱናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ