Home ኪነ-ጥበብ ግጥም የደም ገንቦ (ቦጋለ ዳኜ)
 
የደም ገንቦ (ቦጋለ ዳኜ) Print E-mail
User Rating: / 1
PoorBest 
Art - ግጥም Poem

የደም ገንቦ

ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርኒያ

ኢትዮጵያ የደም ገንቦ ዓይነ-ግቡ እምታስጎመጅ

ያያት ሁሉ የሚመኛት ከአበሻ እስከ ፈረንጅ

ብር አምባሯን እጫካ ውስጥ ያስወሰደች የሴት ሃያጅ

የአሚን ባል ያልገጠማት ይኼ ሁሉ ዘመን ሲባጅ።

ሞትኩልሽ ያለ ሁሉ ደርሶ ላይሆን ጥሩ ወዳጅ

ግሽርጥና እንሶስላ እየሞቀች በእግርና እጅ

ባይንና ጥርስ ሰውን ገዳይ ወንዱን ሁሉ የምታፋጅ።

ካልቀረ መኳኳሏ ግንጥል ጌጥ ስለማይበጅ

ጥሩ አማች እንዲመጣ፤ በጨዋ ደንብ፤

“መጫምያ አርጊ፤

አልቦ አርጊ፤

ኩታ ልበሽ፤

ራስሽን አትጣይ”

ብለው ሲሏት “አሻፈረኝ” የምትል ልጅ።

አቻ ዘር ስታማርጥ ቆማ ቀርታ ከምታረጅ

ምናል አንዱን መርጣ (ሕግ ገብታ) ቤተሰብ ብታደራጅ?

መልከኛ ወንድ መርጦ ማግባት ከሆነባት የዓይን አዋጅ

መልክ ታጥቦ አይጠጣ አይደለ ጠላና ጠጅ።

አሳዳጊ የበደላት ተብላ ስትፈረጅ

ወላጅስ ለምን ይፈር ሲስቅበት ወጪ ወራጅ።

መቀነት ብትፈታ ለሷም ስለሚበጅ

ቤተ ዘመድ እስኪ ይምከር ትጠየቅ በአማላጅ።

ከፊሉ ቤተ ዘመድ ያልተስማማው በዚህ ግዳጅ

ባሌ የምትለው ስላላት ከንፈር ወዳጅ

እሱ እንዲጠልፋት ይመክራል ቆሞ ከደጅ

በዚህ ነገር ያልተስማማው ሌላው ወገን ሰው አናዳጅ

ሞያሌ እግሯን ይዞት ስላተረ እንደ ብጉንጅ

አካሄዷ ሸፋፋ ነው ይላል ትቆነጃጅ

ሆኖም እሷ ስለሆነች ለትዳሯ ዋና ፈራጅ

ዘመድ ሁሉ ሳያገልላት ዓይንሽ ላፈር ብሎ ወግጅ

ይሻላል አንዱን ብትመርጥ ጊዜ ከምትፈጅ።


ቦጋለ ዳኜ

ከካሊፎርኒያ

 

አዲስ ዜናዎችና ጽሑፎች

 

በጽሑፍ መሳተፍ ለምትፈልጉ በሙሉ!

በማናቸውም ጉዳይ ላይ ያለዎትን ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ትችት፣ ግጥም፣ ልብወለድ፣ … በማይክሮሶፍት ወርድ ፕሮግራም በዩኒኮድ ፎንት ጽፈው ከራስዎ ኢ-ሜይል ሳጥን ጽሑፎትን አያይዘው በኢ-ሜይል አድራሻችን 

ethiopiazare@gmail.com ቢልኩልን ለሥራችን ቅልጥፍና ይረዱናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ