Home ኪነ-ጥበብ ግጥም ምነው?! (ጌታቻው አበራ)
 
ምነው?! (ጌታቻው አበራ) Print E-mail
User Rating: / 1
PoorBest 
Art - ግጥም Poem

ምነው?!

ጌታቻው አበራ

እንደሾተላይ ቅርቃር - ልቤ ውስጥ ተሰንቅሮ፣

እንደመጋኛ ውጋት - ክፉኛ ጎኔን ወድሮ፣

ሽብር በሆዴ ነስንሶ - እሚልሰኝ ጧት ማታ፣

ሕመሟ ሕመም ሆኖኝ - ዘወትር እማይገታ፣

ክፉ ዜናዋን ሰምቼ - እንዴትስ ልደር ተኝቼ?

ምነው ስቃይ መከራ - ተሰጠስ ለኔ ባደራ!

 

በፍቅሯ ሰመመን ታብቼ - ከመቃጠል በቀር ሳስቼ፣

ከእኩዮቼስ ተለይቼ - እኔ ከሷ ምን አግኝቼ?!

 

“… ደሞ ጀመረ …” እያሉ - ኮሶ ሲመስል ፊታቸው፣

ባልንጀሮቼ ሲሸሹኝ ልብ-አወቅ የምላቸው፣

ለማን ላውጋው ጭንቀቴን፣

የሚበላኝን ያንጀቴን፤

ለማን ላዋየው? የሷን ነገር፣

ታምቆ በሆዴ ስቸገር፤

 

እናትነቷ የሁላችን - ምን ተገኘ በኔ የተለየ፣

ፍቅሯ ውስጤን ገዝግዞ - መከራዬን እያሳየ፣

ነፍሴ ሐሴት ተነፍጋ - እንዴት ይሁን እኔስ ኑሮዬ?

በቃ በለኝ! ተለመነኝ! የፍጡራን አባት አንድዬ።

 

ምናደረኩህ አምላኬ? ያለማት ገዢ አብዬ፣

ዕድሜ ልኬን ወደ ውስጥ - እንደፈሰሰ እንባዬ፣

ላልታወቀልኝ ኅቡዕ በሽታ - ላልተገኘለት መድኅን ፍዋሴ፣

ምነው? ምን በበደልኩኝ? በቁሟ ትሰቃይ ነፍሴ!

 

በየሄድኩበት ተከትሎ - እያባነነኝ ቅዠቱ፣

ከሌላ እንዳልለምድ ሸብቦ - የናት አንጀት ስስቱ፣

የቀስተ-ደመናዋ አለላ - የሰንደቋ ውበቱ፣

የፍቅሯ ማኅተም ቀለሙ - ምነው በኔ ላይ ፅናቱ?!

 

ቅኔ ምስጢሩ ያልተፈታ፣

ምንድነው የኔ ልዩ ስጦታ?

ያርባ ቀን ዕድሌ የኔ ዕጣ፣

በጥቁር አፈሯ ተከትቤ እምቀጣ፤

ኧረ ባክህ ፈጣሪ?! አድናትና ፈውሰኝ፣

አለበለዚያም “ገላግለኝ”፤

ነባሩን ዘፍግፈህ አውጣና እሚችል አንጀት አስታቅፈኝ፤

ደንዳና ልብ ለግሰኝ።


 

ጌታቻው አበራ

ታህሣሥ ፳፻፪ (ዲሴምበር 2009)

(ይህቺን ግጥም እንድከትብ ሃሳብ ላጫሩብኝ፣ የናት ሀገራቸው ፍቅር እያንገበገባቸው፣ ዘወትር የማይሽር የሚመስለው ሕመሟ ሰቀቀን … እየሆነባቸው ለሚረበሹ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች በሙሉ!)

 

አዲስ ዜናዎችና ጽሑፎች

 

በጽሑፍ መሳተፍ ለምትፈልጉ በሙሉ!

በማናቸውም ጉዳይ ላይ ያለዎትን ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ትችት፣ ግጥም፣ ልብወለድ፣ … በማይክሮሶፍት ወርድ ፕሮግራም በዩኒኮድ ፎንት ጽፈው ከራስዎ ኢ-ሜይል ሳጥን ጽሑፎትን አያይዘው በኢ-ሜይል አድራሻችን 

ethiopiazare@gmail.com ቢልኩልን ለሥራችን ቅልጥፍና ይረዱናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ