Home ኪነ-ጥበብ ግጥም ”ኖረ” (ፊልጶስ)
 
”ኖረ” (ፊልጶስ) Print E-mail
User Rating: / 6
PoorBest 
Art - ግጥም Poem

”ኖረ”

ፊልጶስ ከሆላንድ

በልቶ ጠግቦ አደረ ምንም ሳይርበው

ወይም አልጠግብ ባይ ቁጣን አመመው

ጠፍቶ የሚቀምሰው ወይም ጠኔ ጣለው፤ …

ሲቀረሻ ዋለ ካላቅሙ ጠጥቶ

ወይም ደርቆ ዋለ ጉሮሮው ውሃ አ’ቶ፤ …

ምርጥ - ምርጥ ለበሰ እጅግ አማረበት

ወይ እርቃኑን ሄደ ቡቱቶው አልቆበት፤ …

ሲፈነጥዝ ታየ ደስታ ፈነቀለው

ወይም ኀዘን ችግር ባልንጀራ አ’ረገው፤ …

ህሊናውን ሸጦ - ላላፊ ጥቅም ለውሸት አደረ

ከሕግ በላይ ሆኖ በሥልጣን ባለገ - ፍትህን አሰረ

ወይ ሳያወላውል ጊዜ ሳይለውጠው ከእውነት ጋር አበረ

በአግባቡ ፈረደ - ትህትናን ተሞልቶ ህዝብን አከበረ፤ …

በቁሙ የሚሞት - እየሞተ እሚኖር ፈሪ ሆነ ‘ርብትብት

ወይም ቆራጥ ጀግና ባላማው የፀና - የማይፈራ ሞት፤ …

ት’ግስተኛ አዋቂ እጅግ ደግ የዋህ ነው - የለበሰ ፍቅርን

ወይም ”ጠብ ያለሽ በዳቦ” ችኩል ጨካኝ ይሁን፤ …

ብቻ … በምድር ላይ እስትንፋስ ካለው

እንደ አፈጣጠርም ሥራም ዥንጉርጉር ነው

ከመሸም ከነጋ ውሎ ካደረ ሰው

ስሙ መጠሪያው ለሁሉም የወል ነው

ጥንትም ሆነ ዛሬ ”ኖረ” ነው እሚባለው።


 

ፊልጶስ ከሆላንድ This e-mail address is being protected from spambots, you need JavaScript enabled to view it

 

አዲስ ዜናዎችና ጽሑፎች

 

በጽሑፍ መሳተፍ ለምትፈልጉ በሙሉ!

በማናቸውም ጉዳይ ላይ ያለዎትን ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ትችት፣ ግጥም፣ ልብወለድ፣ … በማይክሮሶፍት ወርድ ፕሮግራም በዩኒኮድ ፎንት ጽፈው ከራስዎ ኢ-ሜይል ሳጥን ጽሑፎትን አያይዘው በኢ-ሜይል አድራሻችን 

ethiopiazare@gmail.com ቢልኩልን ለሥራችን ቅልጥፍና ይረዱናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ