|
ሌቱ እስኪነጋ አንዱዓለም በቀለ - ከስዊዘርላንድ ጆሮ አልሰማ አይል - ብዙ ጉድ ይሰማል፥ ቴዲ ታስሯል ብለው - ሲገርመኝ ሰንብቷል፥ ደግሞ አሁን ተፈታ - ብለው ይነግሩኛል፥ በቃ አሁን ይብቃ - ተዉ ዝም በሉ፥ “የሌባ ዓይነ ደረቅ” - ሆኖ እንጂ ነገሩ፥ ለኔ እንደሚገባኝ - ወዲ ነው ሚስጥሩ፥
እንዴት የታሰረ - ሰው አሰርኩኝ ይላል?! እራሱን ያልፈታ - እንዴት ፈታሁ ይላል?! ቴዲም ይገርመዋል - ይሄን አይነግረንም፥ ሀገር በእስር ሆና - ነፃ ወጣሁ አይልም። ፍትህ በግረሙቅ - የፊጥኝ ተጠፍሮ፥ ሐቅ ገደል ገብቶ - ነፃነት ተቀብሮ፥ ነፃ ሰው ነኝ ብሎ - መች በነፃ ኖሮ፥ ከወገኑ ጋራ - ሁሌ አንጀቱ አሮ። በልጅነት ዕድሜው - ሽማግሌ ሆኖ፥ ሲመክር ኖረ እንጂ - ፍቅር ሠላም ብሎ፥ ቢላችሁን ጣሉ - ሞፈር ያዙ ብሎ። አንድነት እንዲሆን - መለያየት ቀርቶ፥ በዜማው አስውቦ - በቅኔ አዋዝቶ፥ እስላም ክርስቲያኑ - እንዲኖር ተስማምቶ፥ ቤቱ እንደማይጠበን - መከረ እንጂ ተግቶ፥ ላፍታ መች አረፈ - ቴዲ ተመቻችቶ? ብርሃን እንዲሆን - ጨለማው ተገሎ፥ ከወገኑ ጋራ - ወትሮም ወህኒ ሆኖ፥ ወደ አምላክ ጮኸ እንጂ - አይነጋም ወይ ብሎ፥ ነፃ ሰው ነኝ ብሎ - ቴዲ መች ኮብልሎ! እናም ወገግ እስኪል - ሌቱ እስኪነጋ፥ እስኪነጋ በጣም - ብርሃን እስኪወጣ፥ መለከት ተነፍቶ - ትንቢት እስኪፈታ፥ ወደ ምስራቅ ዞረን - እስኪሆን እፎይታ፥ አበባዬሆሽም - እስኪዜም በደስታ፥ “አሳሪ” ነኝ ባዩም - እራሱ እስኪፈታ፥ መቼ ሊዘናጋ - ቴዲ ለአንድ አፍታ፥ ድሮም አልታሰረ - ዛሬም አልተፈታ።
አንዱዓለም በቀለ ከስዊዘርላንድ |