ዋና ገጽ ኪነ-ጥበብ ግጥም እኔና እኔ... (አትክልት አሰፋ መሸሻ)
 
እኔና እኔ... (አትክልት አሰፋ መሸሻ) Print E-mail
User Rating: / 5
PoorBest 

ማንነትን ገልጾ የውስጥን አውጥቶ፣

ንዴትን፣ ብሽቀትን ሁሉንም ጎትቶ፣

በየትኛው መንገድ በየትስ ተጉዞ፣

እንዴት ይገለጻል? የውስጥ ውስጥን መዞ።

እናንተ ንገሩኝ ያጣችሁ የናንተን?

የጋራ ሳይሆኑ... የግል የሆኑትን፣

ሲለዩዋችሁ ጊዜ... ግራ ተጋብታችሁ...

‘ለማንስ ልንገረው... የውስጤን አውጥቼ

እንዴትስ ልግለጸው... ሁሉን አፍረጥርጬ’


ብላችሁ ያላችሁ?

የምትወዱትን ሰው የተነጠቃችሁ፣

እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህት እያላችሁ፣

ልጅን፣ የልጅ ልጅን፣ ወዳጅን ያጣችሁ።

እናንተ ንገሩኝ ምን ይሆን ልምዳችሁ?

በስደት ሰው ሀገር ምን አተረፋችሁ?

ሞቱ ስትባሉ፤ መርዶ ስትሰሙ፣

ዘመድ አዝማዶችን በሞት ስትቀሙ፤

እንዴት ቻላችሁት ከየትስ መጣ አቅሙ።

በተለይ እናንተ ተስፋ የሌላችሁ፣

ሀገር ለመመለስ መንገዱ ተዘግቶ

መውጫ መመለሻ ጎዳናው ታብቶ

‘ዛሬ ነው?... ነገ ነው?... ሀገሬ ‘ምገባ

ጠዋት ወይስ ማታ ጸሀይ የምትወጣ’


ብላችሁ ያላችሁ?


በህልም የምትኖሩ እውን የሌላችሁ፣

የምትወዱትን ሰው የተነጠቃችሁ፣

ማስታመም፣ መጠየቅ፣ ማየት ሳትችሉ

አፈር ገፍቶ ማልበስ ስትከለከሉ...

አጫውቱኝ የናንተን... ምንድን ተሰማችሁ?

መርዶ ብለው ሰዎች ሞትን ሲነግሯችሁ፤

እንዴት ሆናችሁት?፣ ምን አለስ ልባችሁ?።

የኔን አልናገር ተቀብሯል በሆዴ፣

ማስታመምን አልቻልኩ መች ፈቀደ ገዴ

አልቅሸ አይወጣልኝ ሰ’ዎቹ ያዩኛል፤

ብቻየን አልሆነው ‘ጩኸት’ ያስፈራኛል፤

ያቆራምተኛል... ሀዘን ውስጤ ገብቶ

ከእኔው ጋር ሊቀበር... በውስጤ ተዘግቶ


ለአባቴ - ለጋሼ (አሰፋ መሸሻ) መታሰቢያ

ታህሳስ 6 ቀን 2004 ዓ.ም (ዲሴምበር 16/2011)

 

አዲስ ዜናዎችና ጽሑፎች

 
Banner

በጽሑፍ መሳተፍ ለምትፈልጉ በሙሉ!

በማናቸውም ጉዳይ ላይ ያለዎትን ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ትችት፣ ግጥም፣ ልብወለድ፣ … በማይክሮሶፍት ወርድ ፕሮግራም በዩኒኮድ ፎንት ጽፈው ከራስዎ ኢ-ሜይል ሳጥን ጽሑፎትን አያይዘው በኢ-ሜይል አድራሻችን 

ethiopiazare@gmail.com ቢልኩልን ለሥራችን ቅልጥፍና ይረዱናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ