|
ሳላገባት ፈታኝ ዳግማዊ ዳዊት - መስከረም 2002 ዓ.ም.
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it
ጅሉ ማንነቴ - ጉድ አድርጎኝ ሄዶ ልቤ ይጨነቃል - የጠላኝን ወዶ።
የትውልድ አሻራ - ሰፊው ስድስት ኪሎ ምነዋ ጠበብከኝ - ሲጨንቀኝ ዘንድሮ?
ልቤ ተስፋ አይቆርጥ - አላስቀምጥ ቢለኝ ካለችበት ልሄድ - ወሰንኩ ተነሳሁኝ ምሽት አንድ ሰዓት - ከክፍሌ ወጥቸ ማየት ፈለግሁና - ካለችበት ሄጀ ጫማየን ተጫማሁ - ተበጠረ ጠጉሬ ምን አለ ቢቀናኝ - ብትለመን ፍቅሬ። … ከመኝታ ክፍሌ - በጥድፊያ ወጥቸ የሴቶችን ሕንፃ - አሻግሬ አይቸ ድንገት ቆማ ባያት - ብዬ በማሰቤ በግ ተራን ፈተሽኩት - ሁሉንም ቀርቤ።
ራስ መኮንንን - አዳራሹን ሳልፈው ያዩኝ ያክል ሆኖ - የሙት መንፈሣቸው አስታውሶኝ መጸለይ - አንዴ ቆም አልኩና ጀመርኩኝ ጸሎቴን - አምላኬን ልመና ፈጣሪ እንዲሰማ ውስጧን እንዲያዘጋጅ እኔና እርሷነቷ - ሆነን የልብ ወዳጅ። ጸሎቴን ፈጽሜ - ብዬ ዓለም … ወዓለም “አሜን!” አልኩኝና - ገባሁኝ አዘግም ወረድኩ ወደ በሩ - ታጠፍኩ ወደ ግራ ልቤ እሷን ፍለጋ - ዓይኔ ተሰማራ ኬነዲ በሩ ላይ - ከነሣራ ጋራ አየኋት ቅድስቴን - ቆማ ስታወራ።
ፈራ ተባ እያልኩኝ - ወደዚያው አምርቸ ሠላምታ አቀረብኩኝ - እጆቸን ዘርግቸ ሣራ “ሠላም” ብላ - እጇን ስትሰድልኝ ጨበጥኩት ቀኝ እጇን - ጠጋ ስትልልኝ እጀን መለስኩና - ስፈልግ ቀኝ እጇን ቅድስት “ሃይ!” ሳትለኝ - አዞረችው ፊቷን። ብቻችን ሆነን - እኔና ቅድስቴ እንድንነጋገር - ሆነና ምኞቴ ይቅርታ ጠየኳት - ሣራ እንድትለየን ለእኔና ለቅድስት - ዕድል እንድትሰጠን።
“ሠላም” አልኳት ውዴን - መልሷን ባገኝ ብየ ዓይኖቿን በዓይኖቸ - ለምኘ አባብየ። “ተቀልዷል” አለች - ጉንጮቿ እየቀሉ ምን ነካው ብላ ነው - ፍቅሯን ያላመሉ። “ምንድን ነው ችግሩ” - ብየ ብጠይቃት ለካስ የእኔው ጉድ ነው - እርሷን ያበሳጫት ዘመኑ ሆነና - የቡድን ጨዋታ ከሌሎች ሴቶች ጋር - መቃለዴን አይታ የሚወዳት ዓይኔ - ሌላ ሴት አየና የግል ጣፋጭ ፍቅሯ - የቡድን ሆነና ጣዕሙን ማጣቷ ነው - ያበሳጫት ለካ የእኔም ማንነቴ - በቡድን ተለካ፡
“እውነተኛ ፍቅር - አብሮ የሚያረጀው በግል ነው እንጅ - መቸ በቡድን ነው” ብላ ስትቆጣኝ - ዓይኖቿ እንባ ቋጥረው እለምናት ገባሁ - ጥፋቴን አይቸው። “ቅድስት የእኔ እመቤት - የልቤ ፀሐይ ባክሽ ተለመኝ - መጨነቄን እይ ልክ እንደ ድሯችን - እንደ ዓምና ታቻምና አንድ እንሁን ውዴ - ደግመን እንደገና።”
እጇን አወናጭፋ - በድርጊቴም አዝና ትናገር ቀጠለች - ደግማ በጥሞና “እኔን በእኔነቴ - ቅድስት በመሆኔ ብታከብር ብትወደኝ - ደስ ባለኝ እኔ ከሌላው ተምረህ - የአንተ ያልሆነውን ምን ብለህ ሞከርከው - ማፍቀሩን በቡድን ፍቅሬ የግሌ ነው - የግል መብቴ ከዚያ ነው እሚጀመር - የእኔ ማንነቴ ይህን ስለረገጥህ - መቧደንን ወደህ በቃኸኝ ከእንግዲህ - በል እኔም ልቅርብህ።”
ብላ ተለየችኝ - ጨክና ቅድስቴ አስከፍቷት ኖሮ - አዲሱ እኔነቴ ኬነዲ በር ላይ - ባለሁበት ጥላኝ ቅድስቴ ተጓዘች - ሳላገባት ፈታኝ።
መታሳቢያነቱ፣ በኤች.አይ.ቪ. ኤድስ (HIV - AIDS) ሕይወታቸውን ላጡ፣ … እልባት ያላገኙት የቡድንና የግለሰብ መብቶች መልክ ይዘው ትርጉም ያለው ጉዞ በሀገራችን እንዲጀመር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሚታገሉ ሁሉ ይሁንልኝ። ዳግማዊ ዳዊት መስከረም 2002 ዓ.ም.
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it
|