|
ዘፍናችሁ ቅበሩኝ ዳግማዊ ዳዊት መስከረም 2002 ዓ.ም.
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it
ሰውን ሰው አሳዶ - ቢያሳጣው መድረሻ ጭንቅ ብርክ አስይዞ - ፍፁም መተንፈሻ
ሚሊዮኖች ቢያልቁ - በረሃብ በበሽታ ጦርነት ቢመረጥ - በሠላሙ ፋንታ … መስማማት ተጠልቶ - መናቆር ቢሞገስ ቅደሱ ቢረክስ - ርኩሱም ቢቀደስ ሕግ የጉልበት ሆኖ - ፍትህም ተጠልፎ አስታራቂ ጠፍቶ - ዳኝነት ተገፍፎ መስገብገብ ሕግ ሆኖ - ሙስና ተለምዶ ቅጥፈት ተሞካሽቶ - እውነትም ተዋርዶ ቀማኛን ሆነና - የሚሰማ ጆሮ ቁብ የሚለው ጠፋ - የደሃን እሮሮ እጥፍ ድርብ ሆነ - ሰቆቃው ጨመረ ዓይኔን እንባ ሞላው - ልቤ ተሰበረ። አንገቴን ደፍቸ - መሬትን እየጫርኩ መሞት እንደምሻ - ለአምላኬ እየነገርኩ ፀሎቴ ተሰምቶ - አርጎ ሰማይ ሞቴ ደረሰልኝ - ይህን እንዳላይ። ዛሬ መሄጃዬ - ተራዬ ነውና ከየመንደራችሁ - በጠዋት ውጡና ሸኙኝ ጨፍራችሁ - በዘፈን በዜማ ሞትን መርጫለሁ ይህን ከምሰማ። እናቴ አታልቅሽ - አይመታ ደረት አባቴም አትተክዝ - እኔስ ልሂድበት ትቸው የምሄደው - የምተወው ዓለም ከሞት የባሰ እንጅ - የተሻለ አይደለም። ፅድቅና ኩነኔ - ቢኖርም ባይኖርም ለእኔ እዚህ መኖሬ - ከሞት አይሻልም እኔስ በፈጠረኝ - እመካለሁና ሕይወት ይኖረኛል - ገነት እንደገና። አልያም … ሚካኤል ከበሩ - ባይቀበለኝም አቡዬን ተክልዬን - ላያቸው ባልችልም ገነት መግባት ቀርቶ - ገሃነም ብወርድም ቁርጥ ያጠግባልና - አማረ አላማረም ከመሞት መኖርን - በፍፁም አልመርጥም የዚህ ዓለም ኑሮ - የአምሳያዬ ግፉ ሞትን አስመረጠኝ - ተሽሎኝ ማረፉ። እናም አታልቅሱ - አልሰማ ዋይ ዋይታ በምትኩ አሳዩኝ - ዘፈንና እስክስታ ክራር ጽናጽሉ - ከበሮው ይመታ በገና ይደርደር - አስራ ሁለት ተርታ ይነፋ ዋሽንቱ - ሳክስፎን እምቢልታ ወንዶቹ በሆታ - ሴቶቹ በእልልታ የዛሬን - የዛሬን - እኔን ደስ እንዲለኝ ማልቀሱን ተዉና - ዘፍናችሁ ቅበሩኝ።
ዳግማዊ ዳዊት መስከረም 2002 ዓ.ም.
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it
|